በፍቅር እናስታውሰዋለን

In Loving Memory

ግርማ ተክኤ / Girma Tekie

ግርማ ተክኤ Girma Tekie

ከ ጳጉሜ 3 ቀን 1942 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. September 7 1950 – July 8 2026 (Gregorian)

«ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል።»

"I am the resurrection and the life. The one who believes in me will live, even though they die."

ዮሐንስ 11፥25 · John 11:25

ምስጋናWith Gratitude

የምወደውን እና የማከብረውን ባለቤቴን፣ አባታችንን እና ወንድማችንን አቶ ግርማ ተክኤን በክብር ለመሸኘት በአካል ተገኝታችሁ ሐዘናችንን ለተካፈላችሁ ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን በእግዚአብሔር ስም እናቀርባለን።

ጸሎተ ፍትሐቱን ላከናወናችሁልን የደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ቆሞስ አባ ጽጌ-ሥላሴ፣ በኩረ ትህትና ቀሲስ ዘነበ፣ መላእከ ብርሃን መምህር ጥበበሥላሴ፣ መላእከ ይባቤ ቀሲስ ሃብተማርያም፣ እንዲሁም ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መጥተው ላስተማሩልን እና ለመሰከሩልን መምህር ዘላለም ከመላው ቤተሰቡ፣ እንዲሁም ለምናከብራችሁ የቅድስት ሥላሴ ምእመናን በሙሉ — ስለ ፍቅራችሁ እና ስለ አገልግሎታችሁ እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ እንላለን።

ከተለያዩ ግዛቶች እና ሀገራት ረጅም መንገድ ተጉዛችሁ ከጎናችን ለቆማችሁ ዘመዶቻችን እና ወዳጆቻችን፣ መገኘታችሁ ትልቅ መጽናናት ሆኖልናል።

እንዲሁም በቤታችን ሐዘንተኞችን በመቀበል እና በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ሁሉም ነገር በሰላም እና በሥርዓት እንዲፈጸም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ለለፋችሁ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

በአካል መገኘት ባትችሉም በስልክ፣ በመልእክት እና በጸሎት በሐዘናችን ተካፋይ ለሆናችሁ ሁሉ፣ ፍቅራችሁ ደርሶናል፤ ከልብ እናመሰግናለን።

በሕይወቱ ዘመን አብረውት ለቆሙ፣ በሕመሙ ወቅት ለደገፉት፣ እንዲሁም በዚህ የሐዘን ጊዜ ከጎናችን ሆነው ላጽናኑን አብሮ አደጎቹ፣ የመርካቶ እና የልዑል መኮንን ት/ቤት ጉዋደኞቹ፣ የቦልቲሞር ወዳጆቹ፣ የቡና ገበያ ማህበርትኞች እና ለመላው ወዳጅ ዘመድ ቤተሰባችን ምስጋናችን ከልብ ነው። እግዚአብሔር ሁላችሁንም ዋጋችሁን ይክፈላችሁ።

To everyone who came in person to bid a final farewell, with honor, to my beloved and respected husband — our father and our brother — Ato Girma Tekie, and shared in our sorrow: in the name of God, we offer our heartfelt thanks.

To the priests of Debre Birhan Kidist Selassie Church who performed the fithat prayers — Komos Abba Tsige-Selassie, Bekure Tihtina Kesis Zenebe, Melake Birhan Memhir Tibebeselassie, and Melake Yibabe Kesis Habtemariam — to Memhir Zelalem and his whole family, who came from St. Michael Church to teach and bear witness, and to all the beloved faithful of Kidist Selassie — we say: may God reward you for your love and your service.

To our family and friends who traveled from other states and from abroad to stand beside us — your presence has been a great comfort.

And to all who labored tirelessly — receiving mourners at our home and seeing that everything at the funeral service went smoothly — in the name of God, we offer our heartfelt thanks.

To those who could not be with us in person but shared in our mourning by phone, by message, and in prayer — your love reached us, and we thank you from the heart.

To all who stood beside him through his life, cared for him in his illness, and comforted us in this time of mourning — his childhood companions, his friends from Merkato and from the Le'ul Mekonnen School, his Baltimore friends, the members of the Buna Gebeya Mahber, and all our family and friends near and far — our gratitude comes from the heart. May God reward you all.

የሕይወት ታሪክHis Life

አቶ ግርማ ተክኤ ከአባቱ ከፊታውራሪ ተክኤ ጎይቶም እና ከእናቱ ከወ/ሮ ምልዕትፀጋ በእምነት ጳጉሜ 3 ቀን 1942 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አቆጣጠር፣ በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ መርካቶ በሚባለው ሰፈር ተወለደ።

አቶ ግርማ ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በልዑል መኮንን፣ የዛሬው አዲስ ከተማ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን፣ በመቀጠልም በቴሌ ኢንስቲትዩት በመግባት የዲፕሎማ ትምህርቱን በጥሩ ደረጃ ካጠናቀቀ በኋላ ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ተቀጣሪ ሆኖ አገልግሏል። ባሳየው ንቁ ተሳትፎ እና ታማኝነት በተለያዩ የውጪ ሀገራት ባገኘው የትምህርት ዕድሎች በመጠቀም፣ ሀገሩን እና ሕዝቡን ለበርካታ ዓመታት በቅንነት እና በታማኝነት ሲያገለግል ቆይቷል።

አቶ ግርማ በሥራ ባልደረቦቹ እና በአለቆቹ ዘንድ እጅግ የተወደደ እና የተመሰገነ ነበር። ለሁሉም አዛኝ፣ በችግር ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ፣ ከትልቁም ከትንሹም ጋር ተግባብቶ እና ተፋቅሮ የሚኖር፣ ሳቂታ እና ጨዋታ አዋቂ ነበር።

አቶ ግርማ ከልጅነቱ ጀምሮ ከትምህርቱ ባሻገር እጅግ ጎበዝ ኳስ ተጫዋችም ነበር፤ በዚሁ ችሎታውም በወቅቱ ትልቅ ለነበረው ሰላማዊ ውቅያኖስ ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል።

አቶ ግርማ ዕድሜው ለአቅመ አዳም እንደደረሰ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከወ/ሮ ፅጌ በርሄ ጋር በጋብቻ ተጣምሮ የሁለት ወንዶች እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር። አቶ ግርማ በልጆቹ ደስተኛ፣ ሁለት የልጅ ልጆችንም አቅፎ ለመሳም የበቃ፣ ትዳሩን አክባሪ፣ ደግ፣ ርኅሩኅ እና ለሌሎች ባለትዳሮችም ጥሩ ምሳሌ እና አርአያ ሆኖ የሚጠቀስ ሰው ነበር።

አቶ ግርማ ዘመን ሳይሰለጥን ለሴቶች መብት ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር እንደነበር ጓደኞቹ ምስክሮች ናቸው።

አቶ ግርማ ላለፉት 33 ዓመታት በሀገረ አሜሪካ ኑሮን ሀ ብሎ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፣ ሀበሻ ስደተኞችን የአቅሙን ያህል በመርዳት እና ጠቃሚ መረጃዎችን በመስጠት ማኅበረሰቡን ሲያገለግል ኖሯል። የአቶ ግርማ እና የወይዘሮ ፅጌ ቤት መቼም ተዘግቶ አያውቅም፤ እንግዳ ተቀባይ እና የተቸገሩ የሚረዱበት የፍቅር ቤት ነበር።

ከዚህም በዘለቀ ባልቲሞር የሚገኘውን የደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ዋና መሥራቾች ከሆኑት ሰዎች አንዱ አቶ ግርማ ነበር። ቤተ ክርስቲያኑን በፍቅር፣ በሰላም እና በቅንነት ሲያገለግል እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ምእመናን ምስክሮች ናቸው። ቤተ ክርስቲያኑን በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በጉልበት ሳይቀር፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል፣ እቤቱ እስከዋለበት ጊዜ ድረስ ያለመታከት እና ያለመሰልቸት በቅንነት እና በፍቅር አገልግሏል።

መቼም ሞት ለሁላችንም የማይቀር ወደ ዘላለማዊ ቤታችን መሸጋገሪያ መንገድ ነውና፣ ወንድማችን አባታችን ሲያገለግለው የነበረው እግዚአብሔር አምላክ ነፍሱን በቅዱሳኑ እቅፍ እንዲያደርግልን የፈጣሪ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን።

ከባለቤቱ ፅጌ በርሄ እና ከልጆቹ

Ato Girma Tekie was born to his father, Fitawrari Tekie Goytom, and his mother, Weizero Miletsega Beimnet, on Pagume 3, 1942 in the Ethiopian calendar, in Addis Ababa, in the neighborhood known as Merkato.

When he reached school age, Girma completed his primary and secondary education at the Le'ul Mekonnen School — known today as Addis Ketema. He then entered the Telecommunications Institute, where he earned his diploma with distinction, and went on to serve for many years with Ethiopian Telecommunications. Through the dedication and integrity he showed in his work, he earned opportunities to study in several countries abroad, and he continued to serve his country and his people with sincerity and faithfulness for many years.

Girma was deeply loved and admired by his colleagues and superiors alike. Compassionate toward all and quick to come to anyone's aid in times of trouble, he lived in warmth and harmony with young and old — a man of laughter, wit, and good company.

From childhood, alongside his studies, Girma was also a gifted football player, and with that talent he took the field for Selamawi Wukianos ("Pacific"), one of the celebrated teams of the day.

When he came of age, by God's will Girma was joined in marriage to Weizero Tsige Berhe and became the father of two sons and a daughter. He delighted in his children and lived to embrace and kiss two grandchildren. Devoted to his marriage, kind and tender-hearted, he was often named as an example and role model for other couples.

His friends bear witness that, long before the times changed, Girma stood firm in arguing for the rights of women.

For the past 33 years, from the day he began his life anew in America, Girma served his community — helping Habesha immigrants however he could and sharing guidance that would ease their way. The home of Girma and Tsige was never closed: it was a house of love, welcoming to guests and a refuge for those in need.

Beyond all this, Girma was one of the principal founders of Debre Birhan Kidist Selassie (Holy Trinity) Church in Baltimore. The faithful of those years bear witness that he served the church with love, peace, and sincerity — giving his knowledge, his means, and even his own labor, tirelessly and without complaint, until the day his health kept him home.

Death comes to us all; it is the road by which we cross over to our eternal home. May it be the Creator's good will that God, whom our brother and father so faithfully served, receive his soul into the embrace of His saints.

— From his wife, Tsige Berhe, and his children

የቀብር ሥነ ሥርዓትFuneral Service

ሥነ ሥርዓቱ ሐሙስ፣ ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ተከናውኗል። The service took place on Thursday, July 9, 2026.

የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓት

Church Service · 9:00–11:00 AM

ሰዓት፡ ከጠዋቱ 9:00 እስከ 11:00

ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

Debre Berhan Kidist Selassie Ethiopian Orthodox Tewahedo Church

2900 Dunleer Rd.
Dundalk, MD 21222

የቀብር ሥነ ሥርዓት

Burial · 12:00 PM

ሰዓት፡ ከቀኑ 12:00

7250 Washington Blvd.
Elkridge, MD 21075

የሐዘን መርሐ ግብር

Repast · Immediately After Burial

ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ወዲያውኑ

7250 Washington Blvd.
Elkridge, MD 21075

ሥነ ሥርዓቱ በሰላም ተፈጽሟል። ስለ ፍቅራችሁ፣ ጸሎታችሁ እና ድጋፋችሁ ከልብ እናመሰግናለን። The service has concluded in peace. Thank you for your love, prayers, and support.

የመታሰቢያ (የተዝካር) ቀናትMemorial Days

መታሰቢያቀን (ዓ.ም.)Date (Gregorian)
ሦስተኛ ቀን 3rd dayቅዳሜ፣ ሐምሌ 4 ቀን 2018Saturday, July 11, 2026
ሰባተኛ ቀን 7th dayረቡዕ፣ ሐምሌ 8 ቀን 2018Wednesday, July 15, 2026
አሥራ ሁለተኛ ቀን 12th dayሰኞ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2018Monday, July 20, 2026
ሠላሳ 30th dayዓርብ፣ ነሐሴ 1 ቀን 2018Friday, August 7, 2026
አርባ 40th dayሰኞ፣ ነሐሴ 11 ቀን 2018Monday, August 17, 2026
ሰማንያ 80th dayቅዳሜ፣ መስከረም 16 ቀን 2019Saturday, September 26, 2026
ስድስተኛ ወር 6th monthዓርብ፣ ታኅሣሥ 30 ቀን 2019Friday, January 8, 2027
ሙት ዓመት One-year memorialሐሙስ፣ ሐምሌ 1 ቀን 2019Thursday, July 8, 2027

የሐዘን መግለጫ መልእክቶችMessages of Condolence

ትዝታዎን፣ ጸሎትዎን ወይም የመጽናኛ ቃልዎን ከዚህ በታች ያካፍሉን። Share a memory, a prayer, or a word of comfort below.

መልእክትዎ ቤተሰቡ ካየው በኋላ በዚህ ገጽ ላይ ይታያል። Messages appear on this page after the family has reviewed them.